አጽዋማት እና በዓላት (FASTS AND FEASTS)
አጽዋማት
ጾም ማለት መዋል፣ መከልከል፣ መቆየት ማለት ሲሆን ለተወሰኑ ጊዜያት ወይም ወራት ከጥሉላት ምግብ ወይም ከእንስሳት ከሚገኙ ምግቦች መከልከል፣ ለተወሰነ ሰዓት ደግሞ ምንም ሳይበሉ በመቆየት እግዚአብሔርን በማሰብ የምንፈጽመው ነው።
ከዚህም ሌላ ጾም ዐይን ከሚያየው፣ ጀሮም ከሚሰማው፣ አፍ ከሚናገረው፣ እጅ ከሚሠራው ከሰውነት ሕዋሳቶቻችን ሁሉ የኃጢአት ሥራ መቆጠብ መከልከል ማለት ነው።
የጾም ዐይነቶች
የጾም ዐይነቶች ሁለት ሲሆኑ እነርሱም፦
- ሀ/ የዐዋጅ ጾም
- ለ/ የግል/ፈቃድ ጾም
ሀ/ የዐዋጅ ጾም
የዐዋጅ ጾም የሚባለው በዐዋጅ ከሰባት ዓመት በላይ ለሆነ ለሁሉም ኦርቶዶክሳዊ ሰው የሚታወጅ እና በይፋ ሁሉም ተባብሮ የሚጾመው ነው። “በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥” (ኢዩ 2፥15) እንደተባለ በቤተ ክርስቲያን ታውጆ ሥርዓት ተሠርቶለት የሚጾም ስለ ሆነ የዐዋጅ ጾም ይባላል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታውጃቸው እና ሁላችን በጋራ የምንጾማቸው አጽዋማት ሰባት ሲሆኑ እነሱም፡-
፩. ዐቢይ ጾም፦ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአርዓያነት 40 ቀንና 40 ሌሊት የጾመው ጾም ሲሆን በዲያብሎስም ተፈትኖ ድል አድርጎ የጾምን ኀይል አሳይቶናል። እኛም እርሱን አብነት አድርገን ለጾሙ ልዩ ቦታ ሰጥተን እንጾመዋለን።
፪. ጾመ ድኅነት፦ ከበዓለ ሃምሳ ውጭ በየሳምንቱ የምንጾመው የረቡዕ እና ዐርብ ጾም ነው። ረቡዕ አይሁድ ክርስቶስን ይገድሉ ዘንድ ምክራቸውን ያጸኑበት ዕለት ሲሆን ዐርብ ደግሞ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ቅዱስ ሥጋውን ቆርሶ ክቡር ደሙን አፍስሶ ዓለሙን ሁሉ ያዳነበት ዕለት ነው።
፫. ጾመ ገሃድ፦ ገሃድ ማለት መገለጥ፣ መታየት ማለት ሲሆን ይህም የአንድነቱንና የሦስትነቱንምስጢር በገለጸበት በጥምቀቱ ዋዜማ ማለትም ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ ሲውል ስለማይጾም በዋዜማው የሚጾም ጾም ነው።
፬. ጾመ ሐዋርያት፦ ሐዋርያት ወንጌልን ለማስተማር ወደ ዓለም ሲሰማሩ አገልግሎታቸው የተቃና እንዲሆንላቸው ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሳ ከ፶ ቀን በኋላ ከበዓለ ጰራቅሊጦስ ማግስት ጀምረው እስከ ሐምሌ ፭ ድረስ የጾሙት ጾም ነው።
፭. ጾመ ነቢያት፦ ከኅዳር 15 ጀምሮ እስከ ልደት በዓል ድረስ የሚጾመው ሲሆን የነቢያት ትንቢት መፈጸሙን፣ የ፭ሺሕ ፭፻ የመከራ ዘመን ማብቃቱን እያሰብን የምንጾመው ጾም ነው።
፮. ጾመ ነነዌ፦ በየዓመቱ ከዐቢይ ጾም ሁለት ሳምንት ቀድመን ከሰኞ እስከ ረቡዕ ለ፫ ቀናት የምንጾመው ጾም ነው።
፯. ጾመ ፍልሰታ ለማርያም፦ በየዓመቱ ከነሐሴ አንድ ጀምሮ እስከ ዐሥራ ዐምስት ድረስ ለሁለት ሱባኤ የእመቤታችንን በረከት ለማግኘት የምንጾመው ጾም ነው።
ለ/ የግል/ፈቃድ ጾም
የግል ወይም የፈቃድ ጾም የሚባለው በዐዋጅ ሳይታዘዝ በፈቃዳችን የምንጾመው ነው። በቀኖና የሚሰጠን ጾም የሚመደበው ከዚህ ውስጥ ነው። በተለየ ሁኔታ ለራሳችን የምንጾመው ጾምም የፈቃድ ይባላል። ለምሳሌ ጾመ ዮዲት (ጳጕሜን ላይ የሚጾም) እና ጾመ ጽጌ የፈቃድ አጽዋማት ናቸው።
የበዓላት አከባበር ሥርዐት
በዓል (ላት) በቁሙ የደስታ፣ የዕረፍት ቀን፤ በዓመት፣ በወር፣ በሳምንት የሚከበር፤ ያለፈ ነገር የሚታሰብበት ነው። በአጠቃላይ በዓል ማለት ማሰብ፣ መዘከር፣ ማስታወስ የሚል ትርጕም አለው፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ይህም ቀን መታሰቢያ ይኹናችሁ፤ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ኾኖ ለዘለዓለም ታደርጉታላችሁ›› (ዘፀ 12፥14-17፣ ዘሌ 23፥2-4) በማለት በዓል ዘለዓለማዊ መታሰቢያ እንደ ኾነ ተናግሯል። ስለዚህም በዓላት በዓመታት፣ በወራት እና በሳምንታት ዑደት እየተመላለሱ ይከበራሉ፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ የሚከበሩ የኢየሱስ ክርስቶስ በዓላት በሁለት ይከፈላሉ፤ እነርሱም ዐበይት በዓላት እና ንኡሳን በዓላት በመባል ይታወቃሉ።
ዐበይት በዓላት
ዐበይት በዓላት ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት ታላላቅ ሥራዎችን የፈጸመባቸው ናቸው፤ ብዛታቸውም ዘጠኝ ነው። እነርሱም፦
፩. ፅንሰት (ትስብዕት)፦ ብሥራትም ይባላል፤ በዓሉ የሚከበረው መጋቢት 29 ቀን ሲሆን ቅዱስ ገብርኤል ለእመቤታችን የምሥራቹን የተናገረበት እና አካላዊ ቃል የተፀነሰበት ዕለት ነው። (ሉቃ 1፥26-38)
፪. ልደት፦ በዓሉ የሚከበረው ታኅሣሥ 29 ሲሆን በዘመነ ዮሐንስ ግን የዘመነ ሉቃስ ጳጉሜን 6 ቀን ስለምትሆን ልደት ታኅሣሥ 28 ቀን ይሆናል። በዓሉ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን መወለዱን የምናስብበት ነው። (ማቴ 2፥1-12)
፫. ጥምቀት፦ በዓሉ የሚከበረው ጥር 11 ቀን ሲሆን በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን የምናስብበት ነው። (ማቴ 3፥13)
፬. ደብረ ታቦር፦ በዓሉ የሚከበረው ነሐሴ 13 ቀን ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ መግለጡን የምናስብበት ዕለት ነው። (ማቴ 17፥1-14)
፭. ሆሳዕና፦ በዓሉ ከትንሣኤ አንድ ሳምንት ቀድሞ በሚውለው እሑድ የሚከበር ሲሆን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተጭኖ እየተመሰገነ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት ዕለት ነው። (ማቴ 21፥1-11)
፮. ስቅለት፦ በዓሉ ከትንሣኤ በፊት ባለው ዐርብ የሚከበር ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ሊሆን በመስቀል ላይ መሰቀሉን የምናሰብበት ዕለት ነው። (ዮሐ 19፥1)
፯. ትንሣኤ፦ የዐቢይ ጾም ማብቂያ ቀን ሲሆን የሚውለው በዕለተ እሑድ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ መነሳቱን የምናስብበት ነው። (ዮሐ 20፥1)
፰. ዕርገት፦ በዓለ ትንሣኤ በተከበረ በ40ኛው ቀን በዕለተ ሐሙስ ይውላል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በለበሰው ሥጋ ወደ ሰማይ ማረጉን የምናስብበት ነው። (ሉቃ 24፥50፣ ሐዋ 1፥6-11)
፱. ጰራቅሊጦስ፦ በዓለ ትንሣኤ በተከበረ በ50ኛው ቀን ወይም በዓለ ዕርገት በተከበረ በ10ኛው ቀን በዕለተ እሑድ የሚከበር ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደበት ነው። (ሐዋ 2፥1-4)
ንኡሳን በዓላት
ንኡሳን በዓላት ማለት ከዘጠኙ ዐበይት የጌታ በዓላት ቀጥሎ በዓመት የሚከበሩ ማለት ሲሆን እነሱም የሚከተሉት ናቸው።
፩. መስቀል፦ በዓሉ የሚከበረው መስከረም 17 ሲሆን ንግሥት ዕሌኒ መስቀሉን ከተቀበረበት ጉድጓድ ለማውጣት ቁፋሮ ያስጀመረችበት ቀን የሚታሰብበት ነው።
፪. ስብከት፦ ከልደት በፊት ያለው 3ኛ እሑድ ሲሆን በዓሉ ነቢያት እግዚአብሔር ወልድ ይወርዳል፤ ይወለዳል፤ እያሉ ያስተማሩበት፣ ይህ ትምህርታቸው በክርስቶስ እውን እንደሆነ የምናስብበት ነው። (ዮሐ 1፥44)
፫. ብርሃን፦ ከስብከት ቀጥሎ ያለው እሑድ ሲሆን በዓሉ ነቢያት ይወርዳል፤ ይወለዳል፤ ያሉት አማናዊ ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ የሚነገርበት ነው። (ዮሐ 1፥1-19)
፬. ኖላዊ፦ ከብርሃን ቀጥሎ ያለው እሑድ ሲሆን በዓሉ ነቢያት ይወርዳል፤ ይወለዳል፤ ያሉት ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኛ እንደሆነ የሚነገርበት ነው። (ዮሐ 10፥1-22)
፭. ግዝረት፦ በዓሉ ጥር 6 ቀን ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ8ኛው ቀን ሊገረዝ መሄዱ የሚታሰብበት በዓል ነው። (ሉቃ 2፥21)
፮. ቃና ዘገሊላ፦ በዓሉ የሚውለው የካቲት 23 ሲሆን በዓልን ከበዓል ጋር ለማገናኘት በሚል የሚከበረው ጥር 12 ነው። በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ የመጀመሪያውን ተአምር ያደረገበት እና ክብሩን የገለጸበት ነው። (ዮሐ 2፥1-12)
፯. ልደተ ስምዖን፦ በዓሉ የሚከበረው የካቲት 8 ቀን ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በ40 ቀኑ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ አረጋዊ ስምዖን ጌታን ታቅፎ ትንቢት እንደተናገረ የሚታሰብበት ነው። (ሉቃ 2፥25-35)
፰. ደብረ ዘይት፦ የዐቢይ ጾም እኩሌታ ሲሆን እሑድ ላይ ይውላል፤ በዓሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛ ስለ መምጣቱ ያስተማረው እና ስለ ዓለም ፍጻሜ የተናገረው የሚታሰብበት ነው። (ማቴ 24፥1)
፱. መስቀል፦ በዓሉ የሚታሰበው መጋቢት 10 ሲሆን መስቀሉ ከተቀበረበት የወጣበት ነው።
ከዚህ ቀጥሎ የእመቤታችን፣ የመላእክት፣ የቅዱሳን፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታት በዓላት ደግሞ እንደየክብራቸውና ደረጃቸው በዓመትና በወር ይከበራሉ።