በኢትዮጵያ ኦርቶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ታሪክ የወጣቶች ሰንበት ት/ቤት ማቋቋም የተጀመረው ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ የኸውም ከብዙ ዓመታት በፊት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የሃይማኖት ትምህርት ይከታተሉ የነበሩ ወጣቶች “የሥላሴ ማህበር” ተብሎ የሚጠራ አንድ ማህበር መሠረቱ፣ ይህ ማህበር ለወንዶች ብቻ የተቋቋመ ነበር ይሁንና ከጥቂት ዓመታት በኋላ የካቴድራሉ አስተዳደር ወጣት ልጃገረዶችም የራሳቸውን ማህበር መመሥረት እንዳለባቸው አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው ለጸሎትና ለአምልኮ ወደ ካቴድራሉ የሚመጡ ልጃገረዶችን ሰብስቦ እነርሱም የራሳቸውን ማህበር እንዲያቋቁሙ አበረታታቸው በመሆኑም “ማህበረ ክርስቶስ” በሚል መጠሪያ የሚታወቅ ማህበር መሠረቱ፡፡
የእነዚህ ማህበር አባላት የተሻለ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ትምህርት ማግኘት ሲጀምሩ የቤተክርስቲያንን ትምህርት እየተማሩና እያወቁ በመምጣታቸው በተለይም ልጃገረዶች የቤተክርስቲያንን ዜማ በማጥናት በቤ/ክ ውስጥ ከቁርባን በኋላ መዘመር ጀመሩ፡፡ ይህም እንደ አዲስ ክስተት ታይቶ በካህናቱና በምእመናኑ ዘንድ የሚወደድ ሆኖ ተገኘ የእነዚህ ማህበራት ዓላማቸውም የሚከተሉት ነበሩ፡-
- የክርስትና ሃማኖትን መሰረታዊ ዓላማዎች መማርና ማስተባበር፣
- ሰብአዊ ተግባራትን ማካሄድ፣
- የክርስቲያንን ብሔራዊ ባህል መጠበቅ፣
- ወጣት ልጃገረዶች ያለፍርሃት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና ለህበረተሰቡ አገልግሎት የሚስፈልገውን የሥራ አመራር ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ናቸው፡፡