መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች (CHRISTIAN LIVING AND DOCTRINES)
“ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ” (ኢዩ.፩፥፲፬)
ዲያቆን ሰሎሞን እንየው
የካቲት ፲፤ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት
እንኳን ለታላቁ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን! አምላካችን ጾማችንን በሰላም አስጀምሮ በሰላም ያስፈጽመን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን!
ጾም ከሚበላ፣ ከሚጠጣ መቆጠብ፣ መከልከል፣ ከጥሉላት ምግቦች መታቀብ፣ ሕዋሳትንም ከክፉ ነገር መከልከል፣ ዐይን ክፉ ከማየት፣ ጆሮ ክፋ ከመስማት፣ አንደበት ክፋ ከመናገር፣ ኅሊና ክፋ ከማሰብ መከልከል፣ ራስንና ስሜትን ለእግዚአብሔር ማስገዛት ነው።
ርቱዓ ሃይማኖት እንዲህ ይላል “ከጾም የሥጋ ንጽሕና፣ የነፍስ ቅድስናና ድንግልና ይወለዳሉ። ይህች ጾምም የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ መርከብ ናት፤ በውስጧ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ይኖራሉ። ሩቅ ሀገር የሚሄዱት ያለ መርከብ በባሕር ላይ ፈጽሞ መሄድ እንዳይቻላቸው ሁሉ እንዲሁ ስለጽድቅ የሚጓዙትም በመንፈሳዊት ሐመር ካልታሳፈሩ አንዲት እርምጃ ስንኳን መራመድ አይቻላቸውም።” (ርቱዓ ሃይማኖት ገጽ ፺፩-፺፪)
Read More ▼
ጾም ወደ መንፈሳዊት ሀገር መሸጋገርያ ድልድይ ነው። ያች መንፈሳዊት ሀገር ደግሞ መግቢያ በሯ እጅግ የጠበበች፣ ብዙዎች ሊገቡባት የማይችሉ፣ ለተመረጡት እና መመረጣቸውን ለጠበቁ ሁሉ የምትሰጣቸው፣ በጽድቅና በመልካም ምግባር የጸኑ፣ በጾም እና በጸሎት ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው ያስገዙ፣ ሐሳባቸው እንደ እግዚአብሔር ሐሳብ የሆነላቸው ብቻ የሚወርሷት የደስታ እና የምስጋና ሀገር ናት። ጌታችን በጠባቡ በር ግቡ ሲለን ይህን ለመፈጸም ቅጥነተ ኅሊና ያስፈልጋል፡፡ ሐሳባችን አእምሯችን ከወፈረ በጠባቡ መንገድ ማለፍ አይችልምና። ቅጥነተ ኅሊና እንዲኖረን ታድያ ጾም ትልቅ ድርሻ አለው።
ጾም ማለት ሰው ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ፣ ዕረፍታቸው ምስጋናቸው፣ ምስጋናቸው ዕረፍታቸው የሆኑትን መላእክትን የሚመስልበት፣ የነፍስን ቁስል የምታድን፣ የሥጋን ፍላጎት የምታስወግድ፣ የትሕትና መምህር፣ የጸሎት እናት፣ የእንባ መፍለቂያ፣ የበጎ ሥራ ሁሉ መሠረት፣ የሥራ ሁሉ መጀመርያ ናት። (ማቴ.፬፥፩-፬) “እስመ ጾም እማ ለጸሎት ወእኅታ ለአርምሞ ወነቅዓ ለአንብዕ መቅድመ ኩሉ ግብር ሰናይት፤ ጾም ማለት የጸሎት እናት የትሕትና እኅት፣ የእንባ ምንጭ፣የመልካም ሥራ ሁሉ መጀመሪያ ናት ” እንዲል ፈልፈለ ማሕሌት ቅዱስ ያሬድ። ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ የምናስገዛበት ነው። ክርስቲያኖች እውነተኛ ደስታን ከፈለጋችሁ ሥራችሁን በጾም ጀምሩ፤ ጾምን ቀድሱ፤ ጉባዔውን ዐውጁ፤ በጾማችሁ ሁሉንም የስሜት ህዋሳት አሳትፉት።
መጾም ለምን ይጠቅማል?
የጾም ጥቅሟ ብዙ ነው፤ “እንዲህ ነው፤ እንዲያ ነው” ተብሎ ተዘርዝሮ የሚያልቅም አይደለም፡፡ “የአንጾኪያ ቤተ ክርስትያን ነቢያትና መምህራን ሳውልንና በርናባስን ለመሾም ይጾሙና ይጸልዩ ነበር። ይህን ስላደረጉ መንፈስ ቅዱስ ተናገራቸው” እንዲል፡፡ (የሐዋ.፲፫፥፩-፬) ስለዚህ ጾም ይህን ያህል ታላቅ ኀይል ያላት ናት በተለይ ደግሞ ከጸሎት ጋር ስትሆን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምነጋገርባት ነች። ስንጾምም የሚያበረታንን እንጅ የሚያደክመንን እንጀራ አንብላ፤ ሰላም የሚሰጠንን እንጅ ሰላም የሚነሣንን እንጀራ አናዘውትር፤ ለነፍሳችንና ለሥጋችን የሚጠቅም እንጅ በሁለቱም ወገን ደዌ የሚያመጣብንን እንጀራ አንብላ፤ ይኸውም በጾም ወቅት የክርስቶስን ሥጋና ደም መቀበልን ማዘውተር ነው፤ ልባችሁ በፀጋ ቢጸና መልካም ነው እንጅ በመብል አይደለም፤ በዚህ የሚሠሩ አልተጠቀሙምና እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ። (ዕብ ፲፫፥፱)
ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው መግቢያ ላይ “ኩኑ እንከ ከመ ብእሲ ጠቢብ ዘይጸውም ወዘይጼሊ ወያስተሠሪ ኃጢአቱ ሑሩ በጽድቅ ትርከቡ ሠናየ፤ እንደ ሚጾም፣ እንደ ሚጸልይ፣ ኃጢአቱን እንደ ስለ ኃጢአቱ ሥርየትን ለማግኘት እንደሚደክም ሰው ጥበበኛ ሁኑ መልካሙንም እንድታገኙ በእውነት ተመላለሱ” በማለት ጥበበኛ የሚባለው ምን ዓይነት ሰው እንደሆነ ይነግረናል። ከእኔ በላይ ጠቢብ፣ የጥበብ ሰዎች እያላችሁ እራሳችሁን የምትጠሩ ሰዎች በእውነት ጾም ትጾማላችሁን? ጸሎትስ ታደርጋላችሁን? እንግዲያውስ የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነው እንዲል ጠቢባን ሳትሆኑ ሞኞቾ ናችሁ። (፩ኛቆሮ.፫፥፲፱)
ጌታችን የጾመው ፵ ቀን ሆኖ ሳለ ለምን እኛ ፶፭ ቀን እንጾማለን በሚለው ጥያቄ አንድ ሐሳብ እናንሳና ወደ ዐቢይ ጾም የመጀመርያ ሳምንት ዘወረደ እንለፍ። ጌታችን የጾመው ከዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ቅድስት ከሚለው ጀምሮ የሚታሰብ ሲሆን ይህ ሳምንት ግን የንጉሥ ጾም አጃቢ፣ አምላካችን የጾመውን ጾም ለመጾም እንድንበቃ በጾም በጸሎት የምንለምንበት፣ የታላቁ ጾም መቀበያ ነው። ንጉሥ ከእልፍኙ ሲወጣ ከፊትም ከኋላም እንዲታጀብ የንጉሣችን የክርስቶስ ጾምም እንዲሁ ታጅቦ የሚጾም ጠላትን ድል የምናደርግበት ጾም ነው። አንድም “ጾመ ሕርቃል” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የሮም ንጉሥ ሕርቃል በነገሠበት ዘመን የክርስቶስ መስቀል ዳግመኛ ወደ ፋርስ ወርዶ ጠፍቶባቸው ስለነበር ንጉሡ ሕርቃል መስቀሉ እንዲያስመልስላቸው እግዚአብሔር ኃይል እንዲሆነው የጾሙት ጾም ነው። “መስቀል ተረክበ እምዘ ተኀብዐ ወገብረ መድምመ በኢየሩሳሌም ቅድመ ወበፋርስ ዳግመ፤ መስቀል ከጠፋበት ተገኘ፤ መጀመሪያ በኢየሩሳሌም ድንቅ ነገር አደረገ፤ ዳግመኛም በፋርስ” እንዲል፡፡ (ስንክሳር መጋቢት ፲)
ምንጭ፡ ከማህበረ ቅዱሳን ድህረ-ገጽ የተወሰደ