ስለ ገዳሙ (ABOUT US)
በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አጀማመር አጭር ታሪክ
የኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች ቍጥር እጅግ በጣም ጥቂት በነበረበት በ1980ዎቹ አጋማሽ ላይ በወቅቱ ዲያቆን በነበረው በቀሲስ በቀለ አርጋው አሰባሳቢነት በሴንት አንድሪውስ ማዕከል ግቢ ውስጥ ቦታ በመጠየቅ የጸሎት መርሐ ግብር ተጀመረ። ነገር ግን ስብሰቡ የኑፋቄ አመለካከት በነበራቸው ሰዎች በመጠለፉ እና አቅጣጫውን ለማስቀየር በመሞከራቸው ብዙ ሊገፋ ሳይችል ቀርቶ ስብስቡ ስብስቡ ተበተነ፤ መርሐ ግብሩም ተቋረጠ።
ቀሲስ በቀለ አርጋው
ኾኖም ዲያቆን በቀለ አርጋው (በኋላ ቀሲስ) ተስፋ ባለመቁረጥ ያሉትን ጥቂት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በድጋሚ በማፈላለግ እና በማሰባሰብ በየካቲት ወር 1987 ዓ.ም ሴንት አንድሪውስ ማዕከል ግቢ በሚገኘው የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በወቅቱ በነበሩት የግብፅ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መነኩሴ አባ ጴጥሮስ የጸሎት መርሐ ግብር አስጀመረ። በመቀጠልም በኚሁ አባት መልካም ፈቃድ እና ትብብር ዘወትር ዐርብ ከሰዓት በኋላ ከ9-12 ሰዓት የጸሎት መርሐ ግብር በቋሚነት ተጀምሮ ለወራት ቀጠለ።
አባ ጴጥሮስ
በመቀጠልም ስብስቡን የበለጠ ለማጠናከር እና ለማስፋት እንዲቻል በዲያቆን በቀለ አረጋው አሳሳቢነት እና ብርቱ ክትትል የ1987 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ያሉትን እጅግ በጣም ጥቂት ምእመናን በማስተባበር ገንዘብ እንዲያዋጡ በማድረግ አንድ አባት ከአዲስ አበባ እንዲመጡ ለመጠየቅ ታቀደ።
ከዚህም ጋር በተያያዘ ለሚመጡት አባት አቀባበል እና አገልግሎቱንም ለማስፋት የሰንበት ት/ቤት የመዝሙር ክፍል በማቋቋም የሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ተጀመረ።

የሰንበት ት/ቤት የመዝሙር ክፍል – 1987
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
በጥያቄዉም መሠረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የ1987ዓ.ም የትንሣኤን በዓል በቅዳሴ፣ በቡራኬ እና በትምህርተ ወንጌል ከመንፈስ ልጆቻቸው ጋር እንዲያሳልፉ ወደ አቡዳቢ እና አካባቢዋ እንዲመጡ ተደረገ። ይህም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፈር ቀዳጅ የሆነ የታሪክ አሻራ ሲኾን ብፁዕነታቸውም የዐረቡን ምድር የረገጡ የመጀመሪያዉ ሊቀ ጳጳስ ኾኑ።
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
ብፁዕነታቸውም በግብፅ የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሚያዝያ 15/1987 ዓ.ም ሌሊቱን የትንሣኤ በዓልን በቅዳሴ እና በትምህርተ ወንጌል አገልግሎት ባሳላፉ በኹለተኛው ቀን ማክሰኞ ምሽት ሚያዝያ 17/1987 ዓ.ም (እ.ኤ.አ 25 April 1995) በእንግሊዙ የሴንት አንድሪውስ ቤተ ክርስቲያን በተዘጋጀ ሰፊ የወንጌል አገልግሎት መርሐ ግብር ላይ በወቅቱ የነበሩትን አስተባባሪዎች በማሟላት እና በማጠናከር የቤተ ክርስቲያንን ይዘት የተከተለ የመጀመሪያውን የሰበካ ጉባኤ አባላት አስመረጡ።
ይህ የብፁዕነታቸው ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወደ አቡዳቢ እና አካባቢዉ መምጣት እንዲሁም የሰበካ ጉባኤዉ መቋቋም ለአገልግሎቱ ማደግ እና መስፋት መልካም አጋጣሚ በመፍጠሩ የምእመናኑ ቍጥር ከሳምንት ወደ ሳምንት እያደገ በመምጣቱ በቦታ ጥበት ምክንያት መደበኛ መርሐ ግብሩን ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሰፋ ወዳለዉ የግሪክ ቤተ ክርስቲያን በማዛወር መርሐ ግብሩን ዘወትር ዐርብ ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 9 -12 ተጠናክሮ ቀጠለ።
የመጀመሪያው ሰበካ ጉባኤ
ፋዘር እስጢፋኖስ
ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ለቆየዉ አገልግሎታችን ለረጅም ዓመታት ያለ ምንም የአገልግሎት ክፍያ በነጻ እንድንገለገል የፈቀደልን የግሪኩ ቅዱስ ኒቆላስ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን በኹሉም ነገር ታግሰውን ቤተ ክርስቲያንናችን ዛሬ ለደረሰችበት እንድትበቃ ደግሞ የአስተዳዳሪዉ የፋዘር እስጢፋኖስ ድርሻ የጎላ ነው።
ፋዘር እስጢፋኖስ
በመቀጠልም የ1988 ዓ.ም. የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በድጋሚ በልጆቻቸው መሀል እንዲገኙ በመጋበዝ በቅዱስ ፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በመሀከላችን የተገኙ ሲሆን የእርሳቸውም ለሁለተኛ ጊዜ በአቡዳቢ መገኘት ለአገልግሎቱ መስፋት እና ማደግ ጉልህ ድርሻ አበርክቷል፡፡
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
ብፁዕ አቡነ መልከ ፀዴቅ
የ1989 እና 1990 ዓ.ም. የትንሣኤ እና የልደት በዓላትን ቀሲስ ተክለ ጊዮርጊስን ከኬንያ መልአከ ምሕረት ዘውዴን ደግሞ ከአዲስ አበባ በመጋበዝ በደመቀ ኹኔታ በቅዳሴ እና በወንጌል አገልግሎት ማሳለፍ የተቻለ ሲሆን የ1990 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓልን በአቡዳቢ ተገኝተዉ የመንፈስ ልጆቻቸውን በቅዳሴ እንዲያገለግሉ፣ እንዲባርኩ እና እንዲያስተምሩ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ መልካም ፈቃድ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የተላኩት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ነበሩ።
ብፁዕ አቡነ መልከ ፀዴቅ
ቆሞስ አባ ሙሴ (ብፁዕ አቡነ ሙሴ)
ብፁዕነታቸው ከተጣለባቸው ሓላፊነት በተጨማሪ ምእመናኑን በማሰባሰብ ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን የመድኀኔ ዓለም የጽዋ ማኅበር መሥርተው የተመለሱ ሲኾን ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱም በኋላ ስለ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸዉ ቆይታ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረቡት የጽሑፍ ሪፖርት እና ማሳሰቢያ መሠረት በቅዱስ ፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በተባበሩት ዐረብ ኢምሬት የመጀመሪያ የሆኑትን አባት ቆሞስ አባ ሙሴ (ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ) ለአገልግሎት እንዲመደቡ ማስደረግ ችለዋል። ቆሞስ አባ ሙሴም ከ6ወር የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች የአገልግሎት ቆይታ በኋላ ለኤጲስ ቆጶስነት ታጭተው ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ።
ቆሞስ አባ ሙሴ (ብፁዕ አቡነ ሙሴ)
መሪ ጌታ ሀዲስ አዱኛ
ከቆሞስ አባ ሙሴ (ብፁዕ አቡነ ሙሴ) መመለስ በኋላ የተጀመረውን አገልግሎት ለ3 ዓመታት ያህል ከአዲስ አበባ በመጡት በመሪጌታ ሀዲስ አዱኛ ሲከናወን ቆየ።
መሪ ጌታ ሀዲስ አዱኛ
ቆሞስ አባ ተስፋማርያም ላቀ
መሪጌታ ሐዲስ አዱኛ የአገልግሎት ጊዜያቸዉን ጨርሰው ሲመለሱ በምትካቸው በቅዱስ ፓትርያርኩ መልካም ፈቃድ በ1995 ዓ.ም ቆሞስ አባ ተስፋ ማርያም ላቀ ተመደቡ። ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅም ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመቅረብ ከዓመታት በፊት ለአገልግሎት በመጡበት ወቅት የመድኀኔ ዓለምን የጽዋ ማኅበር እንዲቋቋም እና የጽዋ ማኅበሩም ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውሰው የመድኀኔ ዓለም ጽላት በአባ ተስፋ ማርያም ላቀ እንዲላክ የቤተ ክርስቲያኑም ስያሜ መድኀኔ ዓለም እንዲሆን አሳሰቡ።
ማሳሰቢያውም ተቀባይነት አግኝቶ የመድኀኔ ዓለም ጽላት በቆሞስ አባ ተስፋማርያም ላቀ መጥቶ ወደ መንበረ ክብሩ እንዲገባ ሲደረግ ቤተ ክርስቲያኑም አቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለም ተብሎ እንዲሰየም ኾነ። ቆሞስ አባ ተስፋ ማርያም ላቀም ወደ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች ጽላት በማምጣት የመጀመሪያው አባት ሆነዋል።
ቆሞስ አባ ተስፋማርያም ላቀ
ለአገልግሎት የመጡ ሌሎች ሊቃነ ጳጳሳት

ብፁዕ አቡነ ገሪማ

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል

ብፁዕ አቡነ አረጋዊ

ብፁዕ አቡነ መልከፀዴቅ

ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ

ብፁዕ አቡነ ቀለሜንጦስ

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ

ብፁዕ አቡነ ዘካርያስ

ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም
ቆሞስ አባ ሰይፈ ገብርኤል ኦብሰን
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ በ1999 ዓ.ም ኹለተኛዉን ሐዋርያዊ ጉዞ ለማድረግ ወደ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች ሲመጡ ከመጣው ልኡክ ጋር አብረው የመጡት አባታችን ቆሞስ አባ ሰይፈ ገብርኤል ኦብሰን ቤተ ክርስቲያናችንን ባገለገሉበት 6 ዓመታት ውስጥ የሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎቱን በማጠናከር በራሱ አባላት እንዲመራ ኮሚቴ በማስመረጥ፤ በተለይም ወጣት ወንዶች ወደ አገልግሎት እንዲመጡና እንዲበቁም በማድረግ የተምሮ ማስተማር መርሐ ግብር በመቅረፅ አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት፣ መርሐ ግብርን የመምራት እና የስብከት ዘዴዎችን በማስተማር የሰንበት ትምህርት ቤቱን አንድ ምዕራፍ ወደፊት ያሳደገ ሥራ ሠርተዋል።
ቆሞስ አባ ሰይፈ ገብርኤል ኦብሰን
ከዚህም በተጨማሪ በሃይማኖት ከማይመስሏቸው ጋር በሕይወት አጋጣሚ ትዳር መስርተው እና ቤተሰብ አፍርተው የሚኖሩትን በጽዋ ማኅበር በማሰባሰብ ከሃይማኖታቸው እንዳይርቁ በማስተማር እና በማትጋት ትልቅ ሥራ ሠርተዋል።
በአገልግሎት ዘመናቸውም በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በራሷ የሒሳብ ባለሞያዎች የተደረገውን የኦዲት ሥራ አስጀምረው ተከታትለውም ለፍጻሜ አብቅተዋል። ይህም በእርሳቸው የተጣለ መሠረት ፈር ቀዳጅ ሆኖ በአባታችን በቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል የአገልግሎት ዘመንም ኹለተኛዉ የኦዲት ሥራ ተከናውኗል።
አባታችን ወደ ሌላ ሀገር ርቀው ከሄዱም በኋላም በሃይማኖት ካጸኗቸው ልጆቻቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ሳይቋረጥ የቀጠለ ሲኾን ዛሬ ለቤተ ክርስቲያናችን የጀርባ አጥንት ሆነው የሚያገለግሉትን ወጣቶች በሃይማኖት እና ሥነ ምግባር የቀረጹ የቤተ ክርስቲያናችን ባለውለታ ታላቅ አባት ናቸው።
ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል ብርሃነ
በሊባኖስ፣ በተባበሩት ዐረብ ኢሜሬቶች እና አካባቢዉ አህጉረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪ የነበሩት አባታችን ክቡር ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል ደብሩን ለ4 ዓመታት ያህል በአባታዊ ፍቅር፣ በቅንነት እና በትሕትና ሲያገለግሉ ቆይተው ባደረባቸው ሕመም ምክንያት መስከረም 2011 ዓ.ም በሞተሥጋ ተለይተዋል።
ልዑል አምላካችን እግዚአብሔር ለአባታችን ዕረፍተ ነፍስን እንዲያድልልን የቤተ ክርስቲያናችን፣ አብረው ያገለገሉ አባቶች እና የመንፈስ ልጆቻቸው የዘወትር ጸሎት ነው።
ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል ብርሃነ
ዲያቆን ሀይማኖት በላይ
ዲያቆን ሃይማኖት በላይ ፥ በዲያቆን በቀለ አርጋው (አሁን ቀሲስ) መሠረት የተጣለለትን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በኹለት እግሩ እንዲቆም እና ዘላቂነት እንዲኖረው ከሚኖርበት የሻርጃ ከተማ በራሱ የትራንስፖርት ወጪውን እየሸፈነ በየሳምንቱ ዘወትር ዐርብ ጠዋት ሻርጃ አገልግሎ ለምሳው ዕረፍት ሳያሻው ወደ አቡዳቢ በመመላለስ ያገለግል ነበር ።
አንደበተ ርቱዕ የኾነዉ ዲያቆን ሃይማኖት በላይ በጸሎት በስብከት እና አጥንትን በሚያለመልሙ መንፈሳዊ የንስሓ መዝሙሮቹ ለዓመታት የዘለቀ አገልግሎት በማበርከት ቤተ ክርስቲያናችን ዛሬ ለደረሰችበት ደረጃ እንድትደርስ ከፍተኛዉን መሥዋዕትነት የከፈለ የቤተ ክርስቲያናችን አንጋፋ ባለታሪክ አገልጋይ ነው።
ዲያቆን በቀለ አርጋው (ቀሲስ)
ሊቀ ዲያቆን ብርሃኑ ደሳለኝ (ቀሲስ)
ለሃይማኖቱ እና ለቤተ ክርስቲያኑ ያለው ፍቅር ወደር የማይገኝለት ሊቀ ዲያቆን ብርሃኑ ደሳለኝ (ቀሲስ) እንደዛሬው አባቶች ባልነበሩበት የመጀመሪያዎቹ የአገልግሎት ዓመታት ትልቁን ቀንበር በመሸከም የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል ኹልጊዜም የሚጥር አገልጋይ ነበር።
ምንም አባት ያልተገኘበትን የ1989 ዓ.ም የልደት በዓል በቤተ ክርስቲያን ለማክበር የተሰበሰበው ምዕመን ተስፋ ቆርጦ እንዳይበተን በማጽናናት የለሊቱን መርሐ ግብር ለብቻው በጸሎት፣ በትምህርት እና በዝማሬ በመልካም ኹኔታ እንዲያልፍ ያደረገ የቤተ ክርስቲያኒቱ የጭንቅ ጊዜ ልጅ ነው። ከዚህም ባሻገር በአል ዐይን ከተማ በግለሰብ ቤት ይካሄድ ከነበረ የጽዋ ማኅበር መቋቋም እስከ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መጀመር ድረስ ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል።
ዲያቆን ብርሃኑ ደሳለኝ (ቀሲስ)
መጋቤ ስርዐት ደረጀ ክፍሌ (ቀሲስ)
በወቅቱ የነበረውን የአገልጋዮች እጥረት በተወሰነ ደረጃ ለመቀነስ በማሰብ ነዋሪነታቸዉ በዱባይ የሆኑ ለሃይማኖታቸው ቀናዒ በሆኑ ቤተሰቦች የመኖሪያ ፈቃድ ወጥቶለት በዋናነት ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ እንዲሠራ ወደዚህ ሀገር የመጣው መጋቤ ሥርዐት ደረጀ ክፍሌ ዘወትር በየሳምንቱ ዐርብ ወደ አቡዳቢ እየተመላለሰ በቋሚነት ከማገልገሉም ሌላ በብፁዕ አባታችን አቡነ መልከ ጼዴቅ የተመሠረተው የመድኀኔ ዓለም የጽዋ ማኅበር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ክትትል ያደርግ የነበረ ሲኾን የቤተ ክርስቲያንንም አገልግሎት አጠናክሮ እና መስመር አስይዞ ለአገልግሎት ወደ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬቶች ተመድበው ለመጡት ለቆሞስ አባ ሙሴ (በኋላ ብፁዕ አቡነ ሙሴ) ተሸክሞት የነበረውን ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት እና አደራ ያስረከበ አገልጋይ ነው።
መጋቤ ስርዐት ደረጀ ክፍሌ (ቀሲስ)
ዲያቆን ብሩክ ሃለፎም
በአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የአገልግሎት ዘመኑ ኹኔታዎች እንደልብ በማያመቹበት ጊዜያት ኹሉ ጠንክሮ በቤተ ክርስቲያናችን ለክህነተ ዲቁና የበቁ ወጣቶችን በመሰብሰብ በክህነታቸው እና በአገልግሎታቸው ሙሉ እንዲኾኑ ያለዉን ጊዜ ኹሉ ተጠቅሞ በማስተማር እና በማትጋት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብቁ እንዲኾኑ ሃይማኖታዊ ግዴታውን የተወጣ ዕንቍ አገልጋይ ነው።
ዲያቆን ብሩክ ሃለፎም
ቆሞስ አባ ገብረ ሚካኤል (ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ)
የቤተ ከስቲያናችንም አገልግሎት እየሰፋ እና ተጠናክሮ እየኼደ ባለበት ኹኔታ የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ገብረ ሚካኤል ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ ሓላፊነት ተመርጠዉ በኤጲስ ቆጶስነት ማዕረግ በ1998 ዓ.ም. ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ በመባል ተሾመዉ በሊባኖስ፣ በተባበሩት ዐረብ ኢሚሬቶች እና አካባቢዉ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ኾነዉ እንዲያገለግሉ ተሾሙ።
ይህም ብፁዕነታቸውን በዐረቡ ዓለም የመጀመሪያዉ ሊቀ ጳጳስ ሲያደረጋቸዉ ከቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮች ደግሞ ከብፁዕ አቡነ ሙሴ ቀጥሎ ለዚህ ከፍተኛ ማዕረግ የበቁ ኹለተኛዉ ሊቀ ጳጳስ ያደርጋቸዋል። የብፁዕነታቸውም ለዚህ ታላቅ ሓላፊነት መመረጥ ለቤተ ክርስቲያናችንም ኾነ ለአካባቢዉ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲኾን መንበረ ጵጵስናዉም አቡዳቢ እንዲሆን መደረጉ ለደብራችን እድገት የራሱ የኾነ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ
ፋዘር ክላይቭ
ከዚህ ሌላ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዛሬ ለደረሰችበት ምዕራፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱት ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ ያላቸው ፍቅር በቃላት የማይገለጸዉ የእንግሊዙ የሴንት አንድሪው ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩት ፋዘር ክላይቭ በቆይታቸዉ ዘመን በሚያስፈልጉን ኹሉ ከጎናችን የነበሩ፣ የቤተ ክርስቲያኑን ግቢ የራሳችን የኾነ ስሜት እንዲሰማን ያደረጉ የአባቶችን የመኖሪያ ፈቃድ (ቪዛ) በሴንት አንድሪው ቤተ ክርስቲያን እንዲሆን የፈቀዱ፣ ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ከመንግሥት ቦታ ለመጠየቅ በነበረው ሂደት ውስጥ እንደ አንድ ባለጉዳይ አብረውን የተንከራተቱ የምን ጊዜዉም የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለውለታ ናቸው።
ፋዘር ክላይቭ
አገልግሎቱን በዚህ መልክ የቀጠለዉ ደብራችን በ2009 ዓ.ም በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ ካቴድራል ተብሎ ተሰየመ። በ2015 ደግሞ ከሀገሪቱ መንግሥት የራሱ የኾነ የቤተ ክርስቲያን ቦታ አግኝቶ መቃረቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ግንቦት 26/2015 ዓ/ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተባርኮ ስያሜዉም ምስካየ ሕዙናን መድኀኔ ዓለም ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ተብሎ ለአገልግሎት ከበቃ በኋላ ዛሬ በገዳማችን በመደበኛ መርሐ ግብር የሚካፈሉ ከ500 ያላነሱ በበዓላት ደግሞ ቍጥራቸው እስከ 2,000 የሚደርሱ ምእመናንን ያስተናግዳል። የገዳሙም መደበኛ የአገልግሎት መርሐ ግብር ሰፍቶ በሳምንት ኹለት ቀን ቅዳሜና እሑድ መደበኛ ቅዳሴ አለ። በየወሩ ደግሞ በ12፣ በ21፣ በ24 እና በ27 ቅዳሴ ይቀደሳል። በየሳምንቱ ረቡዕ ማታ ደግሞ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር በማካኼድ በአቡዳቢ እና በአካባቢዉ ለሚገኙ ምእመናን መጽናኛ ኾኗል።

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጉብኝት
በተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ ለአቡዳቢ ምስካየ ሕዙናን መድኀኔ ዓለም ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም በአቡዳቢ መንግሥት ሕጋዊ ዕውቅና ለማግኘትና የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ ለማግኘት በተለያየ ወቅት ጥረት ያደረጉና ያገለገሉ፦ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ በአቡዳቢ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ኤምባሲ፣ በየወቅቱ የነበሩ የሰበካ ጉባኤና የሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ አባላት በሙሉ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል፡፡


የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እና የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጉብኝት ወቅት፡፡
አገልግሎት መጀመር የሚያስችል ፈቃድ (license) ማግኘት
በተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስ በአቡዳቢ መንግሥት ለመጀመሪያ ጊዜ ከተሰጠን 17,682 ካሬ መሬት ላይ ቀንሰን የገነባነዉን ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለማስመረቅና አገልግሎት ለማስጀመር ከሚያስፈልጉ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋናው ጉዳይ የዕውቅና ፈቃድና የአገልግሎት ማስጀመሪያ certificate መቀበል ወሳኙ ጉዳይ ነበር። ይህንንም መድኀኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በፈቀደውና በወደደው ጊዜ በዓመታዊ የመታሰቢያ ክብረ በዓሉ ቀን መጋቢት 27/2015 ከአቡዳቢ መንግሥት DCD (Department of community Development) ተቀብለናል።

ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ ከአቡዳቢ መንግሥት DCD (Department of community development) ሃላፊዎች ፈቃድ (license) በተቀበሉበት ወቅት፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ጉብኝት
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በዝግጅት ላይ የሚገኘውን አዲሱን የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ጊዜያዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የአቡዳቢ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር January 17/2023 ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝቱ ወቅትም የአቡዳቢ መንግሥት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰጠውና የቦታው ስፋት 17,682 ካሬ ላይ በተሠራው ጊዜያዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን፤ እንዲሁም በሌሎች አገልግሎት ሰጪ ቤቶች መደሰታቸውን ገልጸዋል ። በመቀጠልም አባቶቻችን በዘመናቸው ኢየሩሳሌም ላይ ቤተ ክርስቲያንን በመሥራት የቤተ ክርስቲያንን እና የኢትዮጵያን ስም እንዳስጠሩት ፤ እኛም በዘመናችን የአቡዳቢ መንግሥት በሰጠን ቦታ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በመሥራት ዳግማዊት ኢየሩሳሌም እናደርጋለን ። ለዚህም የአቡዳቢ መንግሥትና የኢትዮጵያ መንግሥት ሙሉ ድጋፋቸውን ያደርጋሉ በማለት ቃል ገብተዋል።

ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ አዲሱን የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ጊዜያዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በጎበኙበት ወቅት፡፡
ለዚህ ጉብኝት መሳካትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆነው ሙኃዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አስተዋጽኦ ትልቁንና ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል ። ሙኃዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት በቤተ ክርስቲያን ልጅነቱና ቀናኢነቱ በራሱ ተነሳሽነት ሁኔታዎችን በማመቻቸት ጉብኝቱ ውጤት እንዲኖረውና በቀጣይም ምን መሠራት እንዳለበት አቅጣጫ በማመላከት ኃላፊነቱን በሚገባ ተወጥቷል።


ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ የሆነው ሙኃዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አዲሱን የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ጊዜያዊ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን በጎበኙበት ወቅት፡፡
መቃኞ ቤተ ክርስቲያን ምረቃ
ከአቡዳቢ መንግሥት (DCD) የቦታ ባለቤትነትና የአገልግሎት ማስጀመሪያ ፈቃድ ከተቀበልን በኋላ መቃረቢያ ቤተ ክርስቲያኑን ለማስመረቅ የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት ተችሏል ። ከእነዚህም መካከል፦
1. የተለያዩ ንኡሳን ክፍሎች ያሉት የምረቃ በዓል ዝግጅት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በተገቢው ኹኔታ እንዲከናወን ለማድረግ የሚያስችል ዐቢይ ኮሚቴ ማዋቀር፤
2. ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን መጋበዝ፤
3. የአቡዳቢ መንግሥት ተወካዮች፣ አምባሳደሮች፣ የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ሊቃነ ጳጳሳትና የሃይማኖት አባቶችና ልዩ ጥሪ የተደረገላቸው ልዩ ልዩ እንግዶች እንዲገኙ ማድረግ፤
3. ግምቱ እስከ 10,000 የሚደርስ ሕዝብ እንዲገኝና ይህንን ሕዝብ ማስተናገድ የሚያስችል ልዩ ልዩ ሥራን መሥራት ነበር፤
ይህንንና የመሳሰሉትን ሥራዎች በመሥራት በልዑል እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ማኅበረ ካህናት፣ የየሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፣ ግምቱ ከ10,000 በላይ የሆነ ሕዝብ በተገኘበት እንደ ኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ግንቦት 26/2015 ዓ/ም 1,500 ሰው መያዝ የሚችል ጊዜያዊ ቤተ መቅደስ በቅዱስ ፓትርያርኩ ማስመረቅ ተችሏል።


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዜያዊ ቤተ መቅደሱን በመረቁበት ወቅት፡፡
የአቡዳቢ ምስካየ ሕዙናን መድኀኔ ዓለም ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ግዚያዊ ቤተ ክርስቲያኑን ግንቦት 25/2015 ባርከው የአቡዳቢ ደብረ ሰላም መድኀኔ ዓለም ካቴድራል የነበረው የአቡዳቢ ምስካየ ሕዙናን መድኀኔ ዓለም ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ተብሎ በቅዱስነታቸው መልካም ፈቃድ ግንቦት 26/2015 ዓ.ም ተሰይሞ መንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 26/2015 ዓ/ም በመረቁበት ወቅትና ምንፈሳዊ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የአቡዳቢ ምስካየ ሕዙናን መድኀኔ ዓለም ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም የመቃረቢያ/መቃኞ ቤተ ክርስቲያን፡፡