የቤተክርስትያናችን ታሪክ (OUR HISTORY)

የክርስትና እምነት ወደ ኢትዮጵያ መችና እንዴት እንደገባ።

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት ኢትዮጵያ በብሉይ ኪዳን እምነት አምልኮተ እግዚአብሔር የሚፈጸምባት ሀገር ነበረች። የብሉይ ኪዳን እምነት ወደ ሀገራችን የገባው ከክርስቶስ ልደት በፊት በአንድ ሺሕ ዓመት አካባቢ ንግሥተ ሳባ በኢየሩሳሌም ጉብኝት አድርጋ ከንጉሥ ሰሎሞን ጋርም ተነጋግራ ከተመለሰች በኋላ ነው። በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያኒቱ “ጅውዶ ክርስቲያን” ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን የተሸጋገረ ሕዝብ ቤተ ክርስቲያን ትባላለች።

ንግሥተ ሳባ

ከኢትዮጵያ ነገሥታት ኹሉ በሃይማኖቷ እጅግ የላቀች እንደነበረች በብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች የሚነገርላት ንግሥተ ሳባ (1013-982 ዓ.ዓ) ኢትዮጵያንና የመንን በአንድነት ትገዛ ነበር።ይህች ንግሥት በክብረ ነገሥት ማክዳ፣ በመጽሐፈ ነገሥት ንግሥተ ሳባ ተብላ ተጠርታለች። 1ኛ ነገ 10፥1-14 በወንጌል ደግሞ ንግሥተ አዜብ ተብላ ተጠርታለች። ማቴ 12፥42 ሳባ በአኵስም አጠገብ ያለ ቦታ ስም ነው። አዜብ ደግሞ በደቡብና ምዕራብ መካከል ያለ አቅጣጫ ሲኾን ይህም ስም የተሰጣት ከኢየሩሳሌም በአዜብ በኩል የሚገኙ ኢትዮጵያንና የመንን ትገዛ ስለነበረ ነው፡፡

ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊቷ 
ጥበበኛይቱ ንግስት ንግሥተ ሳባ/ማክዳ/አዜብ/
ከሦስት ሺህ ዓመታት በፊት ኢትዮጵያዊቷ ጥበበኛይቱ ንግስት ንግሥተ ሳባ/ማክዳ/አዜብ/

ንግሥተ ሳባ ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት ዘመናት ከነበሩት ነገሥታት በሃይማኖትም ኾነ በሥልጣኔ ዋነኛዋ እንደነበረች የታወቃል። ንግሥት ማክዳ ንግሥተ ሳባ በሚል ስም በአያቶቿ ዙፋን ተቀምጣ ለሠላሳ አንድ ዓመታት አስተዳድራለች። በክብረ ነገሥት እንደተገለጸው በመልኳ፣ በደም ግባቷ እጅግ ያማረች፣ በጥበብና በማስተዋል የተሞላች ነበረች። እሷም እግዚአብሔር በሰጣት ክብርና ብልጥግና፣ በወርቅና በብር በከበሩ ልብሶች፣ በግመሎች፣ በነጋዴዎችም እጅግ የበለጸገች ነበረች፤ ግዛትዋም እጅግ ሰፊ ነበረ፤ በደቡባዊ ምሥራቅ እስከ ማዳጋስካር፣ በስተሰሜንና በስተምዕራብ እስከ ግብጽና እስከ ኖብያ ዳርቻ፣ በስተደቡብ ዛሬ ቢክቶሪያ ኒያንዛ እስከተባለው ባሕር ድረስ ነበር። ነጭ ዐባይ ኒያንዛ ከሚባለው ባሕር ወጥቶ ከጣና ባሕር ከሚወጣዉ ከጥቁር ዐባይ ጋር ካርቱም ላይ ተገናኝቶ የሱዳንና የምስርን (ግብጽ) አገሮች ያጠጣል።

ከክርስቶስ ልደት አንድ ሺሕ ዓመት ያህል ቀደም ብሎ ከነበሩ ገናና ነገሥታት በምትወለደዉ በንግሥተ ሳባ ዘመን ከኢየሩሳሌምና ከዐረብ፣ ከግብጽና ከሕንድም አገሮች ብዙ ነጋዴዎች ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሱ ነበር። እነዚህ ነጋዴዎች በኢትዮጵያ ከሚገኘው ልዩ ልዩ ዕንቍና አልማዝ፣ ወርቅና ሽቱም እየገዙ በየሀገራቸው ስለወሰዱ በዚህ ኹሉ ምክንያት የኢትዮጵያና የንግሥተ ሳባ ዝና በዓለም ኹሉ ተሰማ። ንግሥተ ሳባ ጠንካራ ንግሥት በመሆኗ የንግድ መስመሩ እስከ ምስር (ግብጽ)፣ ኢየሩሳሌምና ሕንድ የሚዘልቀዉ የንግድ ድርጅቷ እንዲስፋፋና እንዲጠናከር አድርጋለች። የንግድ እንቅስቃሴውንም የተመቻቸ ለማድረግ የሚረዷት ሰባ ሦስት መረከቦችና ዐምስት መቶ ኻያ የግመል  መንጋ ነበራት። እነዚህም በታማኝ ሹሟ በታምሪን ሓላፊነት ሥር ነበሩ።

በንግሥተ ሳባ ዘመን የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን በሕገ ኦሪት ለታቦተ ጽዮን ማረፊያ የሚሆን መቅደስ ማሠራት ጀምሮ ነበር። እሱም በተለያዩ ሀገሮች ለሚኖሩ ነጋዴዎች ለመቅደሱ ሥራ ሊጠቅሙ የሚችሉ ብርቅና ድንቅ የኾኑ ነገሮችን ወደ ኢየሩሳሌም እንዲያመጡ፣ ዋጋቸውንም በወርቅና በብር እንደሚከፍል አሳወቀ። በዚህ ጊዜ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም እየተመላለሰ ይነግድ የነበረው ታምሪን የተባለው ነጋዴ ቀይ ወርቅ፣ ዞጴ እና ሌሎችንም የከበሩ ዕቃችን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም በመኼድ ለሰሎሞን ካስረከበ በኋላ ሲመለስ የሰሎሞንን ቤተ መንግሥት ሥነ ሥርዐት ጥበቡንና ክብሩን ኹሉ ለንግሥተ ሳባ ነገራት።

ንግሥተ ሳባም በጆሮዋ የሰማችውን በዐይኗ ዐይታ ለማረጋገጥ በብዙ ወታደርና ደንገጡር ታጅባ ለሰሎሞን የሚቀርበውን ልዩ ልዩ ስጦታ በከብት አስጭና በታምሪን መሪነት ወደ ኢየሩሳለም ወረደች። መጽ.ነገ.ቀዳ 10፥1-12፣ ዜና መዋ.ካል 9፥1 በደረሰችም ጊዜ ንጉሡ ሰሎሞን በክብርና በደስታ ተቀበላት።  እርሷም ከኢትዮጵያ ይዛለት የኼደችውን መቶ ኻያ መክሊት ወርቅ፣ እጅግም ብዙ ሽቱ፣ የከበረ ዕንቍ ሰጠችው። ንጉሡ ሰሎሞንም የተለየ ማረፊያ ቦታ መርጦ ለራሷና ለሰዎቿ ሰጣት።

የሳባ ንግሥት ወደ ሰሎሞን የኼደቺዉ ጥበቡን ለማወቅ ነውና በልብዋ ያለውን ኹሉ አጫወተችው። እሱም የጠየቀቺውን እንቆቅልሽ ኹሉ ፈታላት። ከእርሱ የተሰወረ ነገር አልነበረም። እርሷም አስተዋይና ጥበበኛ እንደመሆኗ የሰሎሞንን ጥበብ ኹሉ ሠርቶትም የነበረውን ቤተ መንግሥት፣ የቤተ መንግሥቱን ሥርዐትና በእግዚአብሔር ቤት የሚያሳርገውን መሥዋዕት ካየች በኋላ እንዲህ አለችው። “ስለ ነገርህና ስለ ጥበብህ በሀገሬ ሳለሁ የሰማሁት ዝና እውነት ነው፤… አንተን የወደደ በእሰራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይኹን፤ እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘለዓለም ወድዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ።” መጽ.ነገ.ቀዳ 10፥6-9

እዚህ ላይ የተጠቀሰው የንግሥተ ሳባ አነጋገር ወደ ሰሎሞን ከመምጣቷ በፊት ገና ከልጅነቷ ጀምሮ ቀደምት ኢትዮጵያውያን በሕገ ልቡና ያመልኩት በነበረው በአንድ አምለክ በእግዚአብሔር ታምን እንደነበረ በግልጽ የሚያስረዳ ነው። ይህ ባይኾን ኖሮ የእስራኤልን አምላክ ስም ጠርታ አታመሰግንም ነበርና።  ይኹንና በኢየሩሳሌም ስድስት ወር በቆየችበት ጊዜ ሕገ ኦሪትን በመስማትና በመማር እምነቷን የበለጠ እንዳጠናከረች እሙን ነው።

በቤተ ክርስቲያናችንና በሀገር የታሪክ ሰነዶች ተጠቅሶ እንደሚገኘው ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም በቆየችበት ጊዜ ንጉሥ ሰሎሞን እና እርሷ ስለ ጥበብ ሲጠያየቁ ባደረጉት መቀራረብ ፀነሰች። ከዚህ በኋላ ልጅህ መኾኑን የምትረዳበት ምልክት ስጠኝ ብላ ከሰሎሞን የጣቱን ወርቅ ተቀብላ በቶሎ ወደ ሀገርዋ ተመለሰች። የኤርትራን ባሕር ተሻግራ በሐማሴን አውራጃ ማይበላ ከሚባለው ቦታ ስትደርስ ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙንም ዕብነ መለክ (የጥበበኛ ልጅ) ብላ ሰየመችው። ይህም ከጊዜ በኋላ ተለውጦ ምኒልክ ተባለ። ከዚያም ጉዞዋን ቀጥላ ከመናገሻ ከተማዋ ከአኵስም ስትደርስ ደማቅ አቀባበል ተደረገላት።

ሰሎሞን ከንግሥተ ሳባ ለመውለድ የወሰነው በሚወለደው ልጅ አማካይነት የአይሁድ እምነት በኢትዮጵያም እንደሚሰበክና እንደሚስፋፋ አስቀድሞ ስለተገለጠለት ነበር። ስለዚህ ከላይ እንደተመለከትነው ንግሥተ ሳባ ኢየሩሳሌም ኼዳ የአንድ አምላክን እምነት አጠናክራ ከተመለሰች በኋላ እውነተኛውን አምላክ በምልዐት ማምለክ ቀጠለች። ዜጎቿም ይህንኑ እምነት አጠንክረው እንዲይዙ አደረገች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኦሪት እምነት እስከ ዘመነ ክርስትና ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ሃይማኖት ኾኖ ኖረ።

ኢትዮጵያዊዉ ጃንደረባ

 “ነዋ ማይ ወመኑ ይከልአኒ ተጠምቆ፤ እነሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ማን ነው?”  የሐ.ሥ 8፥36

የጌታም መልአክ ፊልጶስን ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደኾነ መንገድ ሂድ አለው፤ ተነሥቶም ሄደ፣ እነሆም ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ነግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘቡዋም ሁሉ የሰለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፣ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር፤ መንፈስም ፊልጶስን ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው፤ ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያሰን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው እርሱም የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው፤ ያነብበውም የነበረው የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበር፡-

እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፤ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል እንዲሁ አፉን አልከፈተም፤ በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል?

የኢትዮጵያ ንግሥት ህንደኬ አዛዥና ጃንደረባ ባኮስ
የኢትዮጵያ ንግሥት ህንደኬ አዛዥና ጃንደረባ ባኮስ

ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ እባክህ ነቢዩ ይህን ሰለማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን? ወይስ ስለሌላ አለው። ፊልጶስም መናገር ጀመረ፤ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። በመንገድም ሲሄድ ወደ ውሃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም እነሆ ውሃ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው? አለው። ፊልጶስም በፍጹም ልብህ ብታምን ተፈቅዶአል አለው። መልሶም ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ አምናለሁ አለ። ሠረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ። ፊልጶስና ጃንደረባዉ ኹለቱም ወደ ውሃ ወረዱ፤ አጠመቀውም፤ ከውሃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፈልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባዉም ኹለተኛ አላየውም፤ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና። የሐ.ሥ 8፥26-39 በማለት ወንጌላዊው ሉቃስ እንደተረከው የክርስትና እምነትና ጥምቀት ወደ ኢትዮጵያ የገባው በ34 ዓ.ም በኢትዮጵያ ንግሥት በሕንደኬ ጃንደረባ በባኮስ አማካይነት ነው።

ያጠመቀውም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ወንጌላዊዉ ፈልጶስ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን አምናለሁ፤ የሚለውን የእምነት ፎርሙላ በመናገር የጀመረና ለዓለም ያበረከተ ኢትዮጵያዊዉ ጃንደረባ ባኮስ ነው። አይሁድና ተንባለት እስከ ዛሬ ድረስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ማመን አቅቶዋቸው የተቸገሩበትንና ዓለምን የሚያስቸግሩበትን ክህደትና ኑፋቄ ሳይከተል ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ለጅ መኾኑን አውቆና አምኖ በማሳመን ለወገኖቹ ትክክለኛውን እምነት ስለ ሰበከ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እስከዛሬ ድረስ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑን ታምናለች፤ ትስብካለች፤ ታሳምናለች።

በዘመነ ሐዋርያት የክርስትና እምነትን በመቀበል የመጀመሪያዉ የወንጌል ገበሬ የኾነው ባኮስ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የእምነትና ሥርዐተ አምልኮ ሕንጻ የመሠረት ድንጋይ ነው። ለሐዲስ ኪዳኗ ኢትዮጵያም ዓለም ዐቀፍ ዕውቅናን ያስገኘ የቤተ ክርስቲያናችን መሥራች ነው። ባኮስ በዚህ ሃይማኖታዊ ጉዞዉ የሕገ ኦሪትንና የሕገ ወንጌልን ጽድቅ በአንድ ጉዞ በመፈጸም የራሱንና የሀገሩን ስም በቅዱስ መጽሐፍ ለማስጠራት በቅቱአል።

ባኮስ ወደ ሀገሩ ተመልሶ ከቅዱስ ፊልጶስ ስለ ክርስቶስ የሰማውንና የተረዳውን ለወገኖቹ ኢትዮጵያውያን እንዳስተማረ የጥንት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ አውሳብዮስ ዘቂሳርያ ጽፎአል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረተችዉ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ፊልጶስ የክርስትና አባቷ ስለኾነ በስሙ ቤተ ክርስቲያን ዐንጻ፣ ጽላት ቀርጻ ታከብረዋለች። በጸሎቱና በአማላጅነቱም ትታመናለች። ከቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ማቴዎስ፣ ቅዱስ ናትናኤል፣ ቅዱስ በርተሎሜዎስ እና ቅዱስ ቶማስ በኢትዮጵያ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ወንጌልን እንደ ሰበኩ የቤተ ክርስትያን ታሪክ ጸሓፊዎች እነሩፊኖስና መስክረዋል።

አባ ሰላማ

በ4ኛው መቶ ዓመት ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሾማቸው ከሐዋርያት ሐረገ ክህነት ተያይዞ የመጣ፣ የሐዋርያት ተከታይ የኾነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባናል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ላከች። የእስክንድርያ ፓትርያርክ ቅዱስ አትናቴዎስም ራሱኑ ሾሞ ላከው።

ኢትዮጵያ ክርስትናን የተቀበለችዉ በመጀመሪያዉ ምእተ ዓመት ይኹን እንጂ በሲኖዶስ ሕግ የኤጲስ ቆጶስ መንበር የተሰጣት በ4ኛው ምእተ ዓመት በ330 ዓ.ም ነው። ከኢትዮጵያ ተልኮ ኺዶ ከእስክንድርያዉ ፓትርያርክ ከቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ኹኖ ተሹሞ በመጣው በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መምህርነት በአብርሃና በአጽብሐ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የክርስትና ሃይማኖት በዐዋጅ ተሰብኩዋል።

ቅዱስ አባ ሰላማ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መንበረ ጵጵስናዉን አኵሱም ላይ አድርጎ በሀገራችን የወንጌልን ብርሃን በሰፊው ስለገለጠ ከሣቴ ብርሃን ተባለ። በዚኹ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የታወቀች ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለመኾን መብቃቷን ታሪክ ያስረዳል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ በምልዐት መፈጸም ጀመሩ። ቅዱስ ፍሬምናጦስ በኢትዮጵያ ግዛት በሙሉ የወንጌልን ትምህርት ለማዳረስ የሚረዱት ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾመ። ይልቁንም በዚያ ጊዜ ሊቀ ካህናት የነበረው እንበረምን ሕዝበ ቀድስ ብሎ ኤጲስ ቆጶስነት ሾመው። በሕዝበ ቀድስም ስብከት የኖባና የሳባ፣ የናግራንና የትግራይ፣ የዐማራና የአንጎት፣ የቀጣ፣ የዘበግዱር ሕዝብ በክርስቶስ አምነውና ተጠምቀው ክርስቲያኖች ኾኑ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ከሱርስት፣ ከዕብራይሰጥና ከጽርዕ ወደ ግእዝ ቋንቋ መለሰ/ተረጐመ። የሳባውያንን (ሳባና ግእዝ) የፊደል አቀማመጥ የለወጠውና አዲሱንም ከግራ ወደቀኝ የመጻፍና የማንበብ ዘዴ የፈጠረ እርሱ ነው። ይልቁንም ድምፁን በመከተል ስድስቱን የፊደል ቅርጾች የጨመረ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን እንደኾነ ታሪክ ይናገራል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ መጀመሪያ ፍሬምናጦስ በኋላ አቡነ ሰላማ ክሳቴ ብርሃንየመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጳጳስ መጀመሪያ ፍሬምናጦስ በኋላ አቡነ ሰላማ ክሳቴ ብርሃን

ከቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ሢመተ ጵጵስና ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ታወቀች። ከዚያም ጊዜ አንሥቶ እስከ 20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ከግብጻውያን ብቻ ጰጰሳት እየተሾሙ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ቆይተዋል። ይኹን እንጂ ከኢትዮጵያውያን መካከል ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጳጳስ፣ አቡነ ፊልጶስ ቆሞስ ሆነው እንደተሾሙ ታሪክ ይናገራል።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከጥንታዊት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሥርዐተ እምነት አንድነትና የእኅትማማችነት ኀብረት ስለነበራት ግብጻውያን ጳጳሳት ሥልጣነ ክህነት በመስጠት ብቻ ተወስነው የቀረው የአስተዳደሩና የውስጥ አመራሩ ይዞታ ግን በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ይካኼድ እንደነበረ ታሪክ የማይክደው ሐቅ ነው። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያናችን በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን፣ በሥርዐተ ትምህርትና በባህል ራሱን የቻለ አቋም የነበራትና ያላት መሆኑ የታወቀ ነው።

ከእ.ኤ.አ 1959  ጀምሮ የተሾሙ ፓትርያርኮች

ከእ.ኤ.አ 1959 ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእስክንድርያ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ፓትርያርክ የመሾም ሙሉ ነጻነት (autocephaly) ካገኘች በኋላ ስድስት ፓትርያርኮች ተሹመዋል። ስማቸው እና የአገልግሎት ዘመናቸው የሚከተለው ነው፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ አቡነ ባሲልዮስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባሲልዮስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (1959–1970)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (1971–1976)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖ ትቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (1976–1988)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ትቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (1988–2022)*
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጵውሎስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጵውሎስ ትቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (1992–2012)
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖትብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ትቀዳማዊ፣ የኢትዮጵያ ፓትሪያርክና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት (2013–አሁን ድረስ) 

*ማሳሰቢያ: አቡነ መርቆሬዎስ እና አቡነ ማትያስ ለተወሰነ ጊዜ በአንድ ላይ አገልግለዋል። እ.ኤ.አ 2018 የእርቅ ስምምነት ከተደረገ በኋላ ሁለቱም እውቅና አግኝተው አቡነ መርቆሬዎስ እስከ ዕረፍታቸው ድረስ (እ.ኤ.አ. 2022) ተባባሪ ፓትርያርክ ሆነው አገልግለዋል። አቡነ ማትያስ አሁን የቤተ ክርስቲያኑ ስድስተኛ ፓትርያርክ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ