እምነታችን (OUR FAITH)

መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱሳት መጻሕፍት ኹሉ ምንጭና ራስ ነው። ማንኛውም ትምህርት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ወይም ሥርዐት በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጠቀሰው ጋር የሚጋጭ ከሆነ በቤተ ክርስቲያናችን ተቀባይነት የለውም። የቤተ ክርስቲያናችን የትምህርተ ሃይማኖት ዋና ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የሥርዐትና የታሪክ ዋና ምንጭም መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያዝዘውን የምትፈጽም፣ የምታስተምርና የምትኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊት ቤተ ክርስቲያን ናት። መጽሐፍ ቅዱስንም እንድናነብበውና እንድንማርበት አዘጋጅታ የሰጠችን እርሷው ናት። ቤተ ክርስቲያኒቱ የምትቀበለው የመጽሐፍ ቅዱስ ቍጥር ብዛት ፹፩ (81) ሲሆን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ፵፮ (46) የሐዲስ ኪዳን ደግሞ ፴፭ (35) ናቸው።

የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት

1. ኦሪት ዘፍጥረት
2. ኦሪት ዘፀአት
3. ኦሪት ዘኁልቍ
4. ኦሪት ዘሌዋውያን
5. ኦሪት ዘዳግም
6. መጽሐፈ ኩፋሌ
7. መጽሐፈ ኢያሱ
8. መጽሐፈ መሳፍንት
9. መጽሐፈ ሩት
10. መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ እና ካልእ
11. መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ
12. መጽሐፈ ነገሥት ካልእ
13. መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ
14. መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ (ጸሎተ ምናሴን ጨምሮ)
15. መጽሐፈ ሔኖክ
16. መጽሐፈ ዕዝራ እና መጽሐፈ ነህምያ
17. መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል እና መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ
18. መጽሐፈ ጦቢት
19. መጽሐፈ ዮዲት
20. መጽሐፈ አስቴር
21. መጽሐፈ መቃብያን ቀዳማዊ እና ካልእ
22. መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ
23. መጽሐፈ ኢዮብ
24. መዝሙረ ዳዊት
25. መጽሐፈ ምሳሌ
26. መጽሐፈ ተግሣጽ
27. መጽሐፈ መክብብ
28. መሓልየ መሓልይ ዘሰሎሞን
29. መጽሐፈ ጥበብ
30. መጽሐፈ ሲራክ
31. ትንቢተ ኢሳይያስ
32. ትንቢተ ኤርምያስ፣ ሰቈቃወ ኤርምያስ፣ ተረፈ ኤርምያስ፣ መጽሐፈ ባሮክ እና ተረፈ ባሮክ
33. ትንቢተ ሕዝቅኤል
34. ትንቢተ ዳንኤል፣ መጽሐፈ ሶስና፣ ጸሎተ ሠለስቱ ደቂቅ፣ተረፈ ዳንኤል
35. ትንቢተ ሆሴዕ
36. ትንቢተ አሞጽ
37. ትንቢተ ሚክያስ
38. ትንቢተ ኢዩኤል
39. ትንቢተ አብድዩ
40. ትንቢተ ዮናስ
41. ትንቢተ ናሆም
42. ትንቢተ ዕንባቆም
43. ትንቢተ ሶፎንያስ
44. ትንቢተ ሐጌ
45. ትንቢተ ዘካርያስ
46. ትንቢተ ሚልክያስ

የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት

1. የማቴዎስ ወንጌል
2. የማርቆስ ወንጌል
3. የሉቃስ ወንጌል
4. የዮሐንስ ወንጌል
5. የሐዋርያት ሥራ
6. ወደ ሮሜ ሰዎች
7. የመጀመሪያዪቱ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
8. ኹለተኛዪቱ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
9. ወደ ገላትያ ሰዎች
10. ወደ ኤፌሶን ሰዎች
11. ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች
12. ወደ ቈላስይስ ሰዎች
13. የመጀመሪያዪቱ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች
14. ኹለተኛዪቱ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች
15. የመጀመሪያዪቱ ወደ ጢሞቴዎስ
16. ኹለተኛዪቱ ወደ ጢሞቴዎስ
17. ወደ ቲቶ
18. ወደ ፊልሞና
19. ወደ ዕብራውያን
20. የመጀመሪያዪቱ የቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት
21. ኹለተኛዪቱ የቅዱስ ጴጥሮስ መልእክት
22. የመጀመሪያዪቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልእክት
23. ኹለተኛዪቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልእክት
24. ሦስተኛዪቱ የቅዱስ ዮሐንስ መልእክት
25. የሐዋርያው የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት
26. የሐዋርያው የቅዱስ ይሁዳ መልእክት
27. የዮሐንስ ራዕይ
28. መጽሐፈ ኪዳን ቀዳማዊ
29. መጽሐፈ ኪዳን ካልእ
30. መጽሐፈ ሥርዐተ ጽዮን
31. መጽሐፈ አብጥሊስ
32. መጽሐፈ ግጽው
33. መጽሐፈ ትእዛዝ
34. መጽሐፈ ዲድስቅልያ
35. መጽሐፈ ቀሌምንጦስ

ጸሎተ ሃይማኖት (የሃይማኖት ጸሎት)

“ኹሉን በያዘ ሰማይንና ምድርን የሚታየውንና የማይታየውን በፈጠረ በአንድ አምላክ በእግዚአብሔር አብ እናምናለን። ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስም እናምናለን። ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፤ ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ፤ የተፈጠረ ያይደለ የተወለደ፤ በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል። ኹሉ በእርሱ ኾነ፤ ያለ እርሱ ምንም ምን የኾነ የለም፤ በሰማይም ያለ በምድርም ያለ። ስለ እኛ ስለ ሰዎች ስለመዳናችን ከሰማይ ወረደ። በመንፈስ ቅዱስ ግብር ከቅድስት ድንግል ማርያም ፍጹም ሰው ኾነ። ሰው ኾኖ በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን ስለእኛ ተሰቀለ፤ ታመመ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በቅዱሳት መጻሕፍት እንደተጻፈ። በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ። ዳግመኛም ሕያዋንንና ሙታንን ይገዛ ዘንድ በጌትነት ይመጣል። ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም። ጌታ ማሕየዊ በሚኾን ከአብ በሠረጸ በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን፤ እንሰግድለት እናመሰግነውም ዘንድ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት የተናገረ። ከኹሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰብዋት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም እናምናለን። ኃጢአትን ለማስተሥረይ በአንዲት ጥምቀትም እናምናለን። የሙታንንም መነሣት ተስፋ እናደርጋለን። የሚመጣውንም ሕይወት ለዘለዓለሙ አሜን።”

የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት መሠረቶች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዶግማ ትምህርት የተመሠረተው ከመጽሐፍ ቅዱስ በወጡትና በሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በተደነገጉት የዶግማ ትምህርቶች ላይ ነው። እነሱም ዐምስቱ አእማደ ምሥጢራት ናቸው።

ሀ/ ምሥጢረ ሥላሴ
ሥላሴ ማለት “ሠለሰ ሦስት አደረገ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲኾን ትርጉሙ “ሦስትነት” ማለት ነው። የሥላሴ ሦስትነት በስም፣ በአካል፣ በግብር እና በኩነት ነው።

የስም ሦስትነት፦ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ፤ አንዳቸው በሌላኛው ስም አይጠሩም፤ ስመ ተፋልሶ የለባቸውም።
የአካል ሦስትነት፦ ለአብ፣ ለወልድ፣ ለመንፈስ ቅዱስ ፍጹም አካል፣ ፍጹም ገጽ፣ ፍጹም መልክ አላቸው። ይህ አካል ዝርው (ብትን) ያልሆነ ረቂቅ መንፈሳዊ አካል ነው።
የግብር ሦስትነት፦ አብ ወላዲና አሥራጺ፣ ወልድ ተወላዲ፣ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ (ከአብ የወጣ) ነው።
የኩነት ሦስትነት፦ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ ነው። ይህም አብ በልብ፣ ወልድ በቃል፣ መንፈስ ቅዱስ በእስትንፋስ (ሕይወት) ይመሰላሉ።

የሥላሴ አንድነት፡ በባሕርይ፣ በህልውና፣ በመለኮት፣ በአገዛዝ፣ በሥልጣን፣ በፈቃድ ነው።

ለ/ ምሥጢረ ሥጋዌ
ሥጋዌ ማለት “ተሠገወ ሰው ሆነ” ከሚል የግእዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን ምሥጢረ ሥጋዌ ማለት የአምላክ ሰው መሆን ምሥጢር ማለት ነው። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ልደታት አሉት። እነሱም፤ ቅድመ ዓለም ከአብ ያለ እናት የተወለደው ልደት እና ድኅረ ዓለም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ያለ አባት የተወለደው ልደት ናቸው። ሰው የኾነውም በተዋሕዶ ነው። ሥጋ የሥጋን ባሕርይ ሳይለቅ መለኮትም የመለኮትነትን ባሕርይ ሳይለቅ ማለት ነው። በዚኽም የተነሳ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ነው።

ሐ/ ምሥጢረ ጥምቀት
ጥምቀት ማለት በውሃ መነከር፣ መዘፈቅ ማለት ነው። የጥምቀት መሥራች ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን የተጠመቀው በዘመነ ሉቃስ ማግሰኞ ጥር 11 ቀን ከሌሊቱ በ10፡00 ሰዓት በ30 ዘመኑ በቅዱስ ዮሐንስ እጅ ነው። በጥምቀት ዳግም ልደትን፣ ድኅነትን እና ሥርየተ ኃጢኣትን እናገኛለን። የጥምቀት ዕድሜ ለሕጻናት ወንድ በ40፣ ሴት በሰማንያ ቀን ነው። ዐዋቂዎች ግን ያለ ጊዜ ገደብ በመጡበት ጊዜ ተምረው አምነው ይጠመቃሉ።

መ/ ምሥጢረ ቍርባን
ቍርባን ቃሉ የሱርስት ሲኾን ትርጉሙ መንፈሳዊ አምኃ (ስጦታ)፣ መሥዋዕት፣ መባዕ፣ ለአምላክ የሚቀርብ ማለት ነው። ምሥጢረ ቍርባንን የመሠረተው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል የዘለዓለም ሕይወትን እና ሥርየተ ኃጢአትን እናገኛለን። ጌታችንም “ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው። እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ” (ዮሐ 6፥54) በማለት አስተምሯል።

ሠ/ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን
ትንሣኤ የሚለው ቃል “ተንሥአ” ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙ መነሣት ማለት ነው። “ትንሣኤ ሙታን” ማለት የሙታን መነሣት ማለት ነው። ይኽም ተለያይተው በተለያየ ስፍራ ይኖሩ የነበሩ ነፍስና ሥጋ ተዋሕደው መነሣት፣ ከሞት በኋላ በነፍስና በሥጋ ሕይወት መገኘት ማለት ነው። ይህን ምሥጢር ተስፋ የምናደርገው ሲሆን ክርስቶስ ዳግመኛ ከመጣ በኋላ ለሚኖረው ዘለዓለማዊ ሕይወት መጀመሪያ ነው።

ሦስቱ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መልኪያዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሃይማኖት አስተምህሮዋን የምትለካባቸው ሦስት መመሪያዎች አሏት፤ እነርሱም፦

ሀ/ ዶግማ፡ የግሪክ ቃል ሲኾን እንደ ቤተ ክርስቲያን አተረጓገም የማይለወጥ፣ የማይቀየር፣ የማይሻሻል፣ የማያረጅ መሠረተ እምነት ማለት ነው። ዶግማ የተደነገገ ሳይኾን የተገለጠ ነው። መገኛውም እግዚአብሔር ነው።

ለ/ ቀኖና፡ ይህም የግሪክ ቃል ሲኾን ሕግ፣ ሥርዐት፣ ደንብ፣ መጠን፣ ልክ ማለት ነው። ቀኖና በዋናነት ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ማለት ነው። የጌታ ትእዛዛት በሙሉ (ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ጾም፣ ጸሎት) ዶግማ ሲሆኑ፣ ቀኖና ደግሞ ዝርዝር አፈጻጸሙ ነው።

ሐ/ ትውፊት፡ “ተወፈየ፤ ተቀበለ፣ ተሰጠ” ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ስጦታ፣ ልማድ፣ ትምህርት፣ ወግ፣ ታሪክ ማለት ነው። እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እግዚአብሔር ከፍጥረት መዠመሪያ አንሥቶ በጽሑፍም ያለ ጽሑፍም የገለጠውን እውነት የምናገኘው በትውፊት ውስጥ ነው።